
አሊ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፍያ ሲደርስ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ባሕሩ ጥላሁን፣ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አበበ አማረ፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ፕሮቶኮል ዲፓርትመንት እና የመጽሐፍ ኒስቴር መስሪያ ቤት ተወካዮች አቀባበል አድርገውለታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የቱሪዝም ሚኒስቴር እና የኢትዮጽያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አሊ አህመድ በኢትዮጵያ የሚያደርገው ቆይታ የተሳካ እንዲሆን የጋራ ሥራዎች በማከናወን ላይ ይገኛሉ።

በእንግሊዙ ኖርዊች ሲቲ እየተጫወተ የሚገኘውና በ2026 የፊፋ ዓለም ዋንጫ ለካናዳ ብሔራዊ ቡድን በአራት ጨዋታዎች ላይ የተሳተፈው አሊ አህመድ እስከ ዓለም ዋንጫ ተሳትፎ የደረሰው የእግር ኳስ ጉዞው እና ስኬቶቹ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ከፍተኛ ተነሳሽነት የሚፈጥር ነው።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በዓለም ዙርያ የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውን የሀገራቸውን መለያ ለብሰው እንዲጫወቱ ላለፉት ጊዜያት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ የሚገኝ ሲሆን አሊ አህመድ ምንም እንኳ በሌላ ብሔራዊ ቡድን ማልያ እየተመለከትነው ቢሆንም አሁንም ኢትዮጵያን መወከል የሚችሉ ተሰጥኦዎች በመላው ዓለም እንደሚገኙ ትልቅ ማሳያ ነው።

ፌዴሬሽኑ ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ ጋር ቁርኝች ለመፍጠር ለሚያደርገው ጥረት እና ለቀጣይ አጋርነቶች የአሊ አህመድ አዲስ አበባ መምጣት ትልቅ ምዕራፍ የሚከፍት ነው።
