
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ባሕሩ ጥላሁን ለትውልደ ኢትዮጵያዊው የካናዳ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አሊ አህመድ ወሎ ሰፈር የሚኘው የፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት አስጎብኝተዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈፃሚው በጉብኝቱ ወቅት ከአሊ አህመድ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ በአፍሪካ እግር ኳስ ላይ ስለተጫወተችው ጉልህ ሚና ፤ የአፍሪካ ዋንጫ እና ካፍን ከመመስረት አንስቶ ውድድሩን በማስተናገድ እና ዋንጫ በማንሳት የነበራትን ታሪክ፣ በኢ/እ/ፌ በዋና ፀሐፊነት እንዲሁም የካፍ ኘሬዝዳንትነት ለረጅም ዓመት የመሩት የአፍሪካ እግር ኳስ አባት ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ በካፍ ላይ የነበራቸው ታላቅ አበርክቶ ምን እንደነበረ እንዲሁም አሁን ካፍ ለያዘው ቅርፅ የነበራቸውን ወሳኝ ሚና አስረድተዋል።

ኢትዮጵያውያን እግር ኳስ ተጫዋቾችን በተመለተ ሀገራችን የተሰጥኦ ችግር እንደሌለባትና በይበልጥ ደሞ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው የሚጫወቱበትን ሁኔታ በተመለከተ አሊ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች የመሆን እድሉ ባይገጥመውም ጥሩ ደጋፊ በመሆን ዲያስፖራ ኢንተግሬሽን ኘሮግራምን እንደ ሀገር መዘርጋት እንዲቻል ሌሎች ከኢትዮጵያ ውጪ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን የማነሳሳት ሥራ የመስራት ከፍተኛ ሚና ሊኖረው እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

አሊ አህመድ በትውልደ ኢትዮጵያዊያን ኢንተግሬሽን ኘሮግራም ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ እና በርካታ ባለተሰጥኦ ኢትዮጵያን ተጫዋቾች በውጪ ሀገር እንደሚገኙ ገልጾ በእዚህም አብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን አሳውቋል። እንዲሁም የብሔራዊ ቡድናችን ደጋፊ መሆኑንም ገልፆል።
አሊ አህመድ በኢትዮጵያ ቆይታው የደራርቱ ቱሉ ስፖርት አካዳሚን የጎበኘ ሲሆን በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ የነበረውን ቆይታውን አጠናቆ ለሊት ወደ እንግሊዝ ኖርዊች ይጓዛል።
