
ባለፈው ሳምንት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በተካሄዱ ታላላቅ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ የኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከፍተኛ ፉክክር በማድረግ አበረታችና ደማቅ ውጤቶችን አስመዝግበዋል።
የዋንዳ ዳይመንድ ሊግ 7ኛ ምዕራፍ በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ ሲከናወን፣ አትሌቶቻችን የግላቸውን እና የዓመቱን ፈጣን ሰዓቶች በማሻሻል አንጸባርቀዋል።
ፈጣን ፉክክር በተስተዋለበት የሴቶች 1,500 ሜትር ሦስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተሳተፉ ሲሆን፣አትሌት ፍረወይኒ ኃይሉ የዓመቱን ምርጥ ብቃቷን አሳይታለች።
አትሌት ፍረወይኒ የዓመቱን የራሷን ፈጣን ሰዓት 3:55.92 በመግባት 2ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
አትሌት ሀረገወይን ካላዩ 12ኛ ፣አትሌት አስቴር አረሪ 13ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል ።
በወንዶች 3,000 ሜትር መሰናክል ለመጀመሪያ ጊዜ በዳይመንድ ሊግ መድረክ ብቅ ያለው ወጣት አትሌት ገመቹ ጎዳና፣ የግሉን ምርጥ ሰዓት ባሻሻለበት 8:05.55 ሰከንድ 2ኛ ወጥቷል።
ይህ ውድድር አትሌት ገመቹ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ያደረገው 6ኛ ውድድሩ ነው።
አትሌት ሳሙኤል ፍሬው የዓመቱን ፈጣን ሰዓቱን ባሻሻለበት 8:09.13 ሰከንድ 4ኛ ደረጃ ፣አትሌት አብርሃም ስሜ የዓመቱን ፈጣን ሰዓቱን ባሻሻለበት 8:13.48 ሰከንድ 7ኛ ደረጃ ፣አትሌት ኃይለማርያም አማረ በ8:32.74 ሰከንድ 18ኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል ።
በ5ሺህ ሜትር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አዲሱ ይሁኔ 12ኛ፣አትሌት ሀይሪ በጂጋ 15ኛ፣አትሌት ጌትነት ዋለ 16ኛ እና አትሌት ኩማ ግርማ 19ኛ ሆነው ጨርሰዋል።
በክሮሽያ ዛግሬብ በተካሄደው የጎልድ ደረጃ ውድድር ላይ የኢትዮጵያ አትሌቶች የበላይነታቸውን አረጋግጠዋል።

በሴቶች የ3,000 ሜትር ውድድር አትሌት ንግስቲ ሞላ ውድድሩን በበላይነት ስታጠናቅቅ አትሌት ማስተዋል መሀባው ተከታትላ በመግባት ሁለተኛ ወጥታለች ።
አትሌት ሞሀዲን ወርቁ በወንዶች 1,500 ሜትር አስደናቂ ብቃት በማሳየት እና የግሉን ምርጥ ሰዓት በሆነው 3:32.71 በመግባት 3ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል።
በጋቦኗ የወደብ ከተማ ፖርት ጄንቲል በተካሄደው ዓለም አቀፍ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ላይ አትሌቶቻችን ጠንካራ ፉክክር አድርገዋል።
በሴቶች ዘርፍ ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች ከ2ኛ እስከ 4ኛ ያለውን ተከታታይ ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል።
አትሌት አክሱማዊት እምባዬ በ31:25 ሰከንድ 2ኛ ፣አትሌት አይናለም ደስታ በ31:27 ሰከንድ 3ኛ ፣አትሌት ቦሰና ሙላቴ በ31:38 ሰከንድ 4ኛ ደረጃን ይዘው ፈፅመዋል ።
በወንዶች የ10 ኪሎ ሜትር ፉክክር ላይ ወጣት አትሌቶቻችን ተስፋ ሰጪ ደረጃን ይዘው ገብተዋል።
አትሌት ይስማው ድሉ 4ኛ እና አትሌት ሐጎስ እዮብ 5ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።
