ቺካጎ ማራቶን እና የኢትዮጵያ ፈርጦች ታሪካዊ ትስስር፦ ከነጋሽ አስፋው እስከ ሐዊ ፈይሳ!

0
Screenshot_2026_1008_093724~2

የቺካጎ ማራቶን ፈጣንና ጠፍጣፋ (Flat) መንገድ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን ሰዓቶችና የዓለም ሪኮርዶች የሚሰበሩበት ታላቅ መድረክ ነው። በዚህ አስደናቂ ውድድር ላይ የኢትዮጵያ አትሌቶች ደማቅ ታሪክ የጻፉ ሲሆን፣ የሀገራችንን ሰንደቅ ዓላማ በተደጋጋሚ በኩራት አስከብረዋል።

የዘንድሮውን የ2026 ውድድር ከመጠባበቃችን በፊት፣ ማርካ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያን አትሌቶች የቺካጎ ማራቶን ታሪካዊ አሻራ እንደሚከተለው ወደኋላ መለስ ብሎ ዳስሶታል፦

🥇 ታሪካዊው የመጀመሪያ ድል (እ.ኤ.አ 1990)

በቺካጎ ማራቶን መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በአንደኝነት ያውለበለበው አትሌት ነጋሽ አስፋው ነው። ነጋሽ እ.ኤ.አ በጥቅምት 1990 ዓ.ም በተካሄደው ውድድር የወንዶች አሸናፊ በመሆን የኢትዮጵያውያንን የድል በር በቺካጎ ከፍቷል።

🏃‍♂️ የወንዶች የበላይነት እና የፀጋዬ ከበደ አስደናቂ ሰዓት (እ.ኤ.አ 2012)

እ.ኤ.አ በ2012 ድንቅ ብቃቱን ያሳየው አትሌት ፀጋዬ ከበደ ውድድሩን በ2 ሰዓት ከ04 ደቂቃ ከ38 ሰከንድ (2:04:38) በሆነ አስደናቂ ፍጥነት በማጠናቀቅ የቺካጎ ማራቶንን የወንዶች የኮርስ ሪኮርድ በወቅቱ ሰብሮ በአሸናፊነት አጠናቋል። ከእሱ በተጨማሪ አትሌት ብርሃኑ ለገሰ (እ.ኤ.አ 2018) እና ሌሎችም አትሌቶች በዚሁ ፈጣን መንገድ ላይ የኢትዮጵያን የበላይነት አስመስክረዋል።

🏃‍♀️ የሴቶች ፍጹም ንግሥና፦ ከብርሃኔ አደሬ እስከ ባለፈው ዓመት ድል

በሴቶች ዘርፍ የኢትዮጵያ አትሌቶች በቺካጎ መድረክ ላይ ያላቸው ስም እጅግ ገናና ነው፦

ብርሃኔ አደሬ (እ.ኤ.አ 2006 እና 2007)

ታላቋ አትሌት ብርሃኔ አደሬ የቺካጎን ማራቶን በተከታታይ ሁለት ዓመታት (Back-to-Back) በማሸነፍ ታሪክ ሰርታለች።

አፅደ ባይሳ (እ.ኤ.አ 2010 እና 2012)

አፅደ ባይሳ በተመሳሳይ ውድድሩን ሁለት ጊዜ በማሸነፍ የቺካጎ ንግሥት መሆን ችላለች።

ሐዊ ፈይሳ (እ.ኤ.አ 2025)

ባለፈው ዓመት በተካሄደው ውድድር አትሌት ሐዊ ፈይሳ ድንቅ ብቃቷን በማሳየት የሴቶች ሻምፒዮን መሆንዋ ይታወሳል። ዘንድሮም እሁድ ጥቅምት 11 ቀን ይህንን ታሪካዊ አክሊሏን ለማስጠበቅ ወደ ቺካጎ ትገባለች።

🕊️ የኬልቪን ኪፕተም የማይረሳ የዓለም ሪኮርድ (እ.ኤ.አ 2023)

ስለ ቺካጎ ማራቶን ታሪክ ሲነሳ፣ እ.ኤ.አ በ2023 የወንዶችን የዓለም ሪኮርድ በ2 ሰዓት ከ35 ሰከንድ (2:00:35) የሰበረውና በቅርቡ በሞት ያጣነው ኬንያዊው አትሌት ኬልቪን ኪፕተም ሁሌም በታሪክ ሲታወስ ይኖራል። የዘንድሮው ውድድርም ይህንን ታሪካዊ የዓለም ሪኮርድ ለመስበር በሚያልሙ አትሌቶች ዘንድ ከፍተኛ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የሀገራችን አትሌቶች ዘንድሮም ይህንን ደማቅ ታሪክ ለመድገምና አዳዲስ ድሎችን ለመመዝገብ ዝግጁ ናቸው። ማርካ ኢትዮጵያ እሁድ ጠዋት በሚጀመረው ውድድር ላይ አትሌቶቻችን የሚያስመዘግቡትን ውጤት በቀጥታ ከቺካጎ የሚዲያ ማዕከል እያገኘ ያጋራችኋል።

ዘጋባ፦ ወሰንሰገድ መርሻ (ማርካ ኢትዮጵያ)

🔴 ልዩ መግለጫ ከማርካ ኢትዮጵያ (Marca Ethiopia)!

እሁድ ጥቅምት 11 ቀን 2026 ዓ.ም በታላቅ ጉጉት ለሚጠበቀው የቺካጎ ማራቶን ውድድር፣ ማርካ ኢትዮጵያ ከአዘጋጆቹ (Bank of America Chicago Marathon Media Team) ጋር በቀጥታ በመገናኘት ይፋዊ የሚዲያ ድጋፍ እና ሙሉ ዕውቅና ማግኘቱን በደስታ እንገልጻለን።

በአሜሪካ ኤምባሲ ባጋጠመን የቪዛ ቀጠሮ መዘግየት ምክንያት በቦታው በአካል መገኘት ባንችልም፣ የቺካጎ ማራቶን የሚዲያ አስተባባሪዎች ለሥራችን ካላቸው ትልቅ አክብሮት የተነሳ በቀጥታ ከአዲስ አበባ ሆነን ውድድሩን እንድንዘግብ ልዩ የሚዲያ ማዕከል (Press Room) መግቢያ እና ሙሉ ድጋፍ ሰጥተውናል።

ውድድሩ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ከአዘጋጆቹ ጋር በጋራ በመሆን የሀገራችንን ፈርጦች እያንዳንዱን እርምጃ፣ የደቂቃ ልዩነት እና ትኩስ መረጃዎችን በየሰኮንዱ ወደ እናንተ የምናደርስ ይሆናል። አብራችሁን ሁኑ!

ወሰንሰገድ መርሻ (ማርካ ኢትዮጵያ)

Facebooktwitterlinkedinyoutubetumblrinstagramflickrfoursquaremail
Facebooktwitterredditpinterestlinkedintumblrmail