የካፍ ገለልተኛ ከፍተኛ የባለሞያዎች ቡድን በባህር ዳር ከተማ ስታዲየም ምዘና አከናወነ

ኢትዮጵያ የ2028 አፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ያቀረበችውን ጥያቄ ተከትሎ ካፍ በላከው ገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን አማካኝነት ባሕር ዳር ስታዲየም ያለውን ዝግጅት በጥልቀት ገምግሟል።
በካፍ የተመደቡ ገለልተኛ ከፍተኛ የባለሙያዎች ቡድን በባህር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ በክልሉ እና በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል ተደርጎለታል። በጉብኝቱም ወቅት የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትር አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር)፣ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድ፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን፣ የምኒስቴሩ፣ የክልሉ እና የፌዴሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ከልዑካን ቡድኑ ጋር ተገኝተዋል።

በዕለቱ በተካሄደው የመስክ ምዘና የባለሙያዎች ቡድኑ ስታዲየሙ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለውን ዝግጅት በጥልቀት የተመለከተ ሲሆን፣ በተለይም የመጫወቻ ሜዳ እና የልምምድ ስፍራዎች ጥራት፣ የኮምፒቲሽን ዞን፣ የመልበሻ ክፍሎች እና የጽዳት ሁኔታዎች፣ የሆቴሎች እና የሆስፒታሊቲ ዝግጅቶች እንዲሁም አጠቃላይ የስታዲየሙን የአሰራር መዋቅር ገምግመዋል።
በጉብኝቱ ወቅት ከከተማ አስተዳደሩ እስከ ሁሉም የሚኒስቴሩ እና የክልሉ አካላት በቦታው በመገኘት የስቴዲየሙን አጠቃላይ አሰራርና ክፍሎች ለባለሙያዎቹ ገለጻ አድርገዋል።

ባለሙያዎቹ በበኩላቸው ባዩት ነገር እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን የስታዲየሙ የመጫወቻ ሜዳ፣ የመልበሻ ክፍሎች እና የልምምድ ስፍራዎች ደረጃቸውን የጠበቁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። በተጨማሪም በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ በተለይም የስካይቦክሶች፣ የሆስፒታሊቲ ቦታዎች እና የተለያዩ የስፋትና ማሻሻያ ስራዎች መቼ እንደሚጀምሩና እንደሚጠናቀቁ ጥያቄዎችን በማቅረብ አስፈላጊውን ምላሽና የማስፋፍያ እቅድ ተብራርቶላቸዋል።
በመጨረሻም ያለበትን የጥራት ደረጃ ለረጅም ጊዜ ጠብቆ ማቆየት አስፈላጊ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን መሰል አህጉራዊ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች መብዛት ኢትዮጵያ አህጉራዊ ውድድሮችን የማስተናገድ አቅሟንና የካፍን እምነት የበለጠ እንደሚያሳድገው ተመልክቷል።(ምንጭ ፦ኢትዮጵያ ፉትቦል ፌዴሬሽን)
