በዓለም አትሌቲክስ የ2026 የዓመቱ ምርጥ ቅጽበት ዕጩዎች ይፋ ሆኑ፤ትዕግስት አሠፋ እና ዮሚፍ ቀጀልቻ በዕጩነት ተካተዋል

በወሰንሰገድ መርሻ ደምሴ (ማርካ ኢትዮጵያ ስፖርት ሚዲያ)
ጥቅምት 10 ቀን 2019 ዓ.ም (አዲስ አበባ)
የዓለም አትሌቲክስ ማኅበር (World Athletics) የ2026 የውድድር ዓመት እጅግ ማራኪ፣ ስሜት ቀስቃሽ እና የማይረሱ ሁነቶችን ለመሸለም ያዘጋጀውን አዲስ የደጋፊዎች “የዓመቱ ምርጥ ቅጽበት” (Moment of the Year) ሽልማት 18 ዕጩዎችን ይፋ አደርጓል።የዓለም አትሌቲክስ ማኅበር (World Athletics) ለዝግጅት ክፍላችን በኢሜል በላከው መግለጫ፤ በዚህ ታሪካዊና ለመጀመሪያ ጊዜ በሚሰጠው አዲስ ዓለም አቀፍ የክብር ሽልማት ውስጥ የኢትዮጵያ ስም በጉልህ እንዲነሳ ያደረጉት ድንቅ አትሌቶቻችን ትዕግስት አሠፋ እና ዮሚፍ ቀጀልቻ በዕጩነት መካተታቸው ታውቋል።
ይህ አዲስ የሽልማት ዘርፍ የተዘጋጀው ከአንድ ተራ የውድድር ውጤት ባለፈ፣ በመላው ዓለም በሚገኙ ስፖርት አፍቃሪዎችና ተመልካቾች ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃትንና መነሳሳትን የፈጠሩ ድንቅ የስፖርት ቅጽበቶችን መርጦ እውቅና ለመስጠት ነው።

የኢትዮጵያውያን ኮከቦች ታሪካዊ የዓለም ሪከርድ ቅጽበቶች
በዕጩነት ከተካተቱት 18 ታላላቅ የዓለም አትሌቲክስ ስኬቶች መካከል የሁለቱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አስገራሚ የዓለም ሪከርዶች በቀዳሚነት ተጠቃሽ ሆነዋል፦
የትዕግስት አሠፋ የለንደን ማራቶን ድንቅ ገፅታ፦ አትሌት ትዕግስት አሠፋ በለንደን ማራቶን ሴቶች ብቻ በተወዳደረችበት ልዩ መርሃ-ግብር (Women-only) 2:15:41 በሆነ አስደናቂ ሰዓት በመግባት ያስመዘገበችው አዲስ የዓለም ማራቶን ሪከርድ በዓመቱ ደማቅ ቅጽበትነቱ በዕጩነት ቀርባለች።
የዮሚፍ ቀጀልቻ የቦይነስ አይሬስ ታሪክ፦ በአርጀንቲና የቦይነስ አይሬስ በተካሄደው የዓለም ግማሽ ማራቶን ውድድር ላይ አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ 56:51 በሆነ አስገራሚ ፍጥነት በመጨረስ የሰበረው አዲስ የዓለም ሪከርድ በዕጩነት ውስጥ መካተት ችሏል።
ዓለምን ያስደመሙ ሌሎች ዋና ዋና ዕጩዎች
ከኢትዮጵያውያኑ በተጨማሪ በዕጩነት ዝርዝር ውስጥ የተካተቱትና በውድድር ዓመቱ በአትሌቲክሱ ዓለም ትልቅ ስም ካስገኙ አትሌቶች መካከል
ሳባስቲያን ሳዌ (ኬንያ)፦ በለንደን ማራቶን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከሁለት ሰዓት በታች በሆነ 1:59:30 የዓለም ማራቶን ሪከርድን የሰበረበት ቅጽበት።
አግሄስ ንጌቲች (ኬንያ)፦ በሴቶች ብቻ ውድድር የ 1:05:15 የዓለም ግማሽ ማራቶን ሪከርድ በማስመዝገብ የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀችበት ድል።
ሞንዶ ዱፕላንቲስ እና ኢማኑኤል ካራሊስ (ዙሪክ)፦ በላስቲክ ምርኩዝ ዝላይ ውድድር ላይ ዱፕላንቲስ 6.25 ሜትር፣ ካራሊስ ደግሞ 6.20 ሜትር በመዝለል ያደረጉት እጅግ አስደናቂ የዕርስ በዕርስ ፉክክር።
ሙሉ የምርጫ ሥልጣን ለደጋፊዎች መሆንና ፤ የድምፅ አሰጣጡ ሁኔታ
ይህንን ሽልማት ልዩ የሚያደርገው የመጨረሻዎቹን ዕጩዎች የመምረጥ ሙሉ ሥልጣን ለአትሌቲክስ ደጋፊዎች መሰጠቱ ነው። የ World Athletics App በመጫን፣ በመተግበሪያው ዋና ገፅ ላይ የሚገኘውን የሽልማት ማውጫ (Awards tab) በመክፈት ደጋፊዎች ለሚወዱት አትሌትና ቅጽበት በቀጥታ ድምፅ መስጠት ይችላሉ።
የሽልማቱ የጊዜ ሰሌዳ መዋቅር፦
ጥቅምት 16 ቀን 2019 ዓ.ም (October 26, 2026)፦ የደጋፊዎች የድምፅ አሰጣጥ ሂደት በይፋ ይዘጋል።
ጥቅምት 24 ቀን 2019 ዓ.ም (November 3, 2026)፦ በደጋፊዎች ድምፅ የተመረጡት የመጨረሻዎቹ ዕጩዎች (Shortlist) ለሕዝብ ይፋ ይደረጋሉ።
ኅዳር 20 ቀን 2019 ዓ.ም (November 29, 2026)፦ በሞናኮ በሚካሄደው ደማቅ የዓለም አትሌቲክስ ኮከቦች ሽልማት (World Athletics Awards) መድረክ ላይ፣ የባለሙያዎች ቡድን ከመጨረሻዎቹ ዕጩዎች መካከለ የመጀመሪያውን ታሪካዊ አሸናፊ ይፋ እንደሚደረግ ተገልጿል።
(ማርካ ኢትዮጵያ ስፖርት ሚዲያ)
