
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ የእግር ኳስ ውድድሮች ላይ በጨዋታ አመራሮች ላይ የሚፈጸሙ አካላዊ ጥቃቶችን የሚያሳዩ ምስሎች በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በስፋት ሲሰራጩ እየተመለከትን እንገኛለን። እነዚህ አሳዛኝ ድርጊቶች በወቅቱ፣ በጥብቅ እና በተቀናጀ መልኩ መቆጣጠር ካልተቻለ በእግር ኳሳችን ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት ከፍተኛ ነው።
የጨዋታ አመራሮች የእግር ኳስ ውድድሮች በሕግ፣ በፍትሃዊነት እና በስፖርታዊ ሥነ-ምግባር እንዲመሩ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ ባለሙያዎች ናቸው። በመሆኑም ደህንነታቸው አስተማማኝ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ ወደ ውድድር እንዳይመደቡ በቂ ጥንቃቄ ማድረግ፣ ለእግር ኳስ ቤተሰቡ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ማከናወን እና በእነርሱ ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በሕግ አግባብ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ወሳኝ ነው።
ይህንን ችግር በጋራ ኃላፊነት እና በተቀናጀ አሰራር ማስቆም ካልቻልን፣ ለወደፊት ተስፋ የሚሆኑ ወጣት የጨዋታ አመራሮችን ለማፍራት የምናደርገውን ጥረት ከፍተኛ ፈተና ውስጥ ይከተዋል።
የጨዋታ አመራሮች የእግር ኳስ ልማት ዋና አካል ናቸው። የእነርሱን ክብር፣ ደህንነት እና መብት መጠበቅ የዛሬን እና የነገን እግር ኳስ መጠበቅ ማለት ነው።
በመሆኑም በየደረጃው የምትገኙ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች፣ የዳኞች ኮሚቴዎች እና ሁሉም የእግር ኳስ ቤተሰብ ይህንን ጉዳይ በከፍተኛ አፅንኦት በመያዝ፣ የጨዋታ አመራሮችን ለመጠበቅ የየራሳችንን ኃላፊነት በመወጣት የእግር ኳስ ዳኝነት ሙያን እና የስፖርቱን ዕድገት በጋራ እንድናሳድግ ጥሪ እናቀርባለን።
ለዘላቂ የእግር ኳስ ልማት፣ የጨዋታ አመራሮችን ክብርና ደህንነት በጋራ እንጠብቅ በማለት ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ አሳውቋል
