
የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ዓመታዊ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዷል።
ለኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነት ድሬዳዋን በመወከል በእጩነት የቀረቡት አቶ ቢኒያም ነገሱ በ14 ድምፅ አሸናፊ ሆነዋል።

መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤው የበፊቱን ጠቅላላ ጉባኤ ቃለ-ጉባኤን መርምሮ በማፅደቅ በ2017፣ በ2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት፣ በ2016 እና በ2017 በጀት አመት የኦዲት ሪፖርት ላይ መክሯል።
በሌላ በኩል በ2019 በጀት ዓመት እቅድ፣ በተሻሻለው የፋይናንስ መመሪያ እንዲሁም በፕሬዚዳንትና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫ ላይ በአጀንዳነት ተወያይቷል።
መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤው የቀረቡትን አጀንዳዎች መነሻ በማድረግ ፌዴሬሽኑ በበጀት አመቱ ያከናወናቸው ሀገር አቀፍና አለም አቀፍ ውድድሮች በስኬት ጉባኤው መክሮበታል።
ፌዴሬሽኑ በቀጣይ የክትትልና ድጋፍሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት፣ የትጥቅ አቅርቦት የተሻለ ሥራ መስራት ላይ በትኩረት እንዲሰራ በውይይቱ ተነስቷል።
እንዲሁም በክልልና ከተማ አስተዳደር ደረጃ ክለቦችን ማቋቋምና ተተኪዎችን ማፍራት፣ ክለቦችን ማደራጀት፣ የውድድር ፕሮግራም ማዘጋጀት እና የፋይናስ ምንጭን ማጠናከር ላይ በልዩ ሁኔታ መስራት እንዳለበት ጉባኤው አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽንን ለቀጣይ አራት አመታት በፕሬዚዳንትነት የሚመሩትን አቶ ቢኒያም ነገሱ ጨምሮ ስድስት ስራ አስፈፃሚዎችን መርጧል።
የስፖርት ማህበራት በየአመቱ መደበኛ ጉባኤያቸውን ማካሄድ ግደታ መሆኑን ያስገነዘበት በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ማህበራት ምዝገባ፣ ድጋፍ ቁጥጥር መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ዳኒኤል ዳኜ ናቸው።
አዲሱ አዋጅ ቀደም ሲል በነበሩት የአሰራር ክፍተቶች ዙሪያ ሰፊ ትምህርት የተወሰደበት መሆኑን ያስገነዘቡት አቶ ዳኒኤል አዋጁ በርካታ መዋቅራዊ እና የአሰራር ስርአቶችን ይዞ እንደሚመጣ ገልፀዋል።

ባለፉት የምርጫ ሂደቶች ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት በቀጣይ የሚኖሩ የምርጫ ስርዓቶች እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄና ቁጥጥር እንደሚደረግባቸውም ተናግረዋል።
አዲሱ አዋጅ ከላይ እስከ ታች ባለው መዋቅር ውስጥ የሚገኙ የስፖርት አካላት ከዚህ ቀደም ይፈጸሙ የነበሩ ስህተቶችንና ግድፈቶችን በግልጽ ለይቶ በማውጣት የአሰራር ተጠያቂነት እንዲሰፍን የሚያስገድድ እንደሆነም ገልፀዋል።
ሥራ አስፈፃሚው አክለው ማንኛውም የስፖርት ባለሙያ ወይም አካል ድምጽ የመስጠት መብት የሚኖረው በስርዓቱ በተደራጀ ክለብ ስር ሲታቀፍ ብቻ እንደሆነ የአዋጁን ድንጋጌ አመላክተዋል።
