
የአፍሪካ ቼስ ኮንፌዴሬሽን ሁሉም አባል ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች በተገኙበት ጠቅላላ ጉባኤውን በአዲስ አበባ ከተማ ስካይ ላይት ሆቴል አካሄዷል።
ሁለት አጀንዳዎች ላይ በትኩረት መክሮ የቀጣይ አራት ዓመታት መሪውን የመረጠው የአፍሪካ ቼስ ኮንፌዴሬሽን ጉባዔ የ2025/26 የአፈፃፀም ሪፖርቱን እና የፋይናንስ ሪፖርቱን ለጉባዔተኛው ለውይይት አቅርቦ አስተያየት በማሰጠት አፅድቋል።

ጉባዔው ቀጥሎ ሲውል በሚቀጥሉት አራት ዓመታት የአፍሪካ ቼስ ኮንፌዴሬሸንን በፕሬዚዳንትነትና በዞን መሪነት የሚመሩ መሪዎች ምርጫን በማካሄድ ኬኒያዊውን በርናንድ ዋስዋ ዋንጃላን በፕሬዚዳንትነት በመምረጥ ለአራት ዓመት ሾሟል በተመሳሳይ በአፍሪካ የተደራጁ አምስት ዞኖችን የሚመሩ አዳዲስ መሪዎችንም መርጧል።

በ10ኛው የአፍሪካ ቼስ ኮንፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊ የሆኑት የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ተሾመ በቀለ ስለጉባዔው በሰጡት አሰተያየት ሀገራችን ጉባኤውን በማስተናገዷ በርካታ ጠቀሜታዎች ያስገኘላት መሆኑን አንስተው ለአብነትም በጉባዔው በመዲናችን አዲስ አበባ የአፍሪካ የቼስ ኮንፌዴሬሸን ቢሮ የሚከፈት መሆኑ ቃል የተገባበት እንደሆነ አንስተዋል።
አስከትለው አቶ ተሾመ በቀለ የአፍሪካ ቼስ ኮንፌዴሬሸን ቢሮ በመዲናችን ሲከፈት ሀገራችን የቼስ ስፖርት ማዕከል እንድትሆን እድል ይዞላት የሚመጣ መሆኑን በመግለፅ ህብረተሰቡ የቼስ ስፖርት ንቃተ ህሊናን የሚጨምር፣ ምክንያታዊ አስተሳሰብ የሚያዳብር፣ የእውቀት ቅበላ የሚያሳድግ እና በስፖርታዊ ጨዋነት የሚከወን ስፖርት መሆኑን በመገንዘብ ለእድገቱ የበኩሉን አሰተዋፅኦ እንዲያበረክት ጥሪ አስተላልፈዋል።

በተያያዘ በአዲስ አበባ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሰባት ሀገራት የተሳተፉበት እና ላለፉት 7 ቀናት የተካሄደው የአፍሪካ ዞን 4.4 ቼስ ውድድር በትናንትናው ቀን ሲጠናቀቅ በውድድሩ በወንዶች :-
1ኛ/ ማዳጋስካር
2ኛ/ ኡጋንዳ
3ኛ/ ኢትዮጵያ በመሆን ሲያጠናቅቁ በሴቶች፦
1ኛ/ ኬንያ
2ኛ/ ኬንያ
3ኛ/ ኢትዮጵያ
በመውጣት ውድድሩን ሲያጠናቅቁ ለኢትዮጵያ የነሐስ ሜዳልያ አሸናፊ የሆኑት ስፖርተኞች በወንዶች ለይኩን መስፍን በሴቶች ደግሞ ሰላማዊት ስለሺ መሆናቸው ታውቋል።
ከአንድ ሳምንት በላይ ሲካሄድ በቆየው ውድድር ኢትዮጵያ ውድድር የማዘጋጀት አቅሟ ማደጉ የተረጋገጠበት እና የውድድሩ ተሳታፊ ሀገራትም በውድድሩ ደስተኛ እንደነበሩ ሀሳብ የሰጡበት ሆኗል።
