
የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን 20ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በሀርሞኒ ሆቴል አካሂዷል።
መደበኛ ጉባኤው አቶ እያሱ ወሰንን የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አድርጎ መርጧል።
የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ባካሄደው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ያለፈውን ጉባኤ ቃለ ጉባኤ በማፅደቅ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ መክሯል።
መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤው በበጀት ዓመቱ እቅድ አፈፃፀም፣ በተሻሻለው የፋይናንስ መመሪያ፣ እንዲሁም የፕሬዚዳንትና የሥራ አስፈፃሚ ምርጫ በአጀንዳነት ይዞ ከመከረባቸው አጀንዳዎች መካከል ይገኙበታል።

ፌዴሬሽኑ በባለፉት ዓመታት ዓለምአቀፍ ውድድሮች በሀገር ውስጥ እንዲካሄዱ ማድረጉ እና የተሻለ ዓለምአቀፍ ግንኙነቶች መፍጠር መቻሉ በጥንካሬ ጉባኤው ያነሳቸው ጉዳዮች ናቸው።
በሌላ መልኩ ፌዴሬሽኑ የቦክስ ቁሳቁሶች ድጋፍ ጨምሮ ስልጠናዎችን መስጠት መቻሉ በስኬት ተነስተዋል።
የዳኞች የውሳኔ አሰጣጥ አሰራር ሥርዓት መስተካከል እንዳለበት ጉባኤው አፅዕኖት የሰጠበት ጉዳይ ሲሆን የአሰልጣኝነት የፈቃድ አሰጣጥ መስተካከል እንዳለበትም ጉባኤው ተወያይቶበታል።
የቦክስ ስፖርትን በተሻለ መንገድ ለማስቀጠል ከክልልና ከተማ አስተዳደር ጋር ቅንጅታዊ ሥራዎች መኖር እንዳለበት ያመላከተው ጉባኤው ክለቦችን ማስፋፋት ትኩረት እንዲሰጥም መደበኛ ጉባኤው አቅጣጫ ሰጥቶበታል።
የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የሚያካሄዳቸው ዓመታዊ ውድድሮችና ስልጠናዎች በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እውቅና ሊኖራቸው እንደሚገባ በጉባኤው ተመላክቷል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሆነው በ9 ድምፅ ዳግም የተመረጡት አቶ እያሱ ወሰን በጉባኤው ማጠቃላያ ባስተላለፉት መልዕክት አዲሱ አመራር የስፖርቱን ደረጃ ለማሳደግ በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል።
ብቃት ያላቸውን አትሌቶች ለማፍራት እና ፌዴሬሽኑን በፋይናንስ ራሱን ወደ መቻል ለማሸጋገር ያለመ ሰፊ እቅድ ይዞ እንደሚስራም ገልፀዋል።
በተለይም በኦሊምፒክ እና በዓለምአቀፍ መድረኮች የሀገራችንን ሰንደቅዓላማ ከፍ አድርገው የሚያውለበልቡ አትሌቶችን ለማፍራት ከስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰሩ አቶ እያሱ አስታውቀዋል።
ከዚህ ቀደም ከክልሎች ጋር የነበረውን ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር ተገቢውን ድጋፍ በመስጠትና የእለት ተእለት የጋራ ግብ በመቅረጽ የቦክስ ስፖርት በመላው ሀገሪቱ እንዲስፋፋ ይደረጋልም ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።
አትሌቶች ሁልጊዜም በከፍተኛ ዝግጅት እና ብቃት ውስጥ እንዲቆዩ ለማድረግ በየሳምንቱ እና በየጊዜው በመላ ሀገሪቱ ውድድሮች እንደሚካሄዱ አመላክተዋል።
የጋራ ጥረትን በመጠቀም ቦክስ ሀገራችን የምትኮራበት ስፖርት እንዲሆን ጠንክረው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ከበደ እጅጉ በበኩላቸው በስፖርት ማህበራት ህግ መሠረት የስፖርት ማህበራት በወቅቱ ጉባኤያቸውን ማካሄድ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የስፖርት ማህበራት በተሰጣቸው እውቅና መሠረት የስፖርት ማህበራት የፋይናንስ አቅማቸውን በማጠናከር ሀገራቸውን በዓለምአቀፍ ደረጃ የሚያስጠሩና የሚወክሉ ስፖርተኞችን ማፍራት ቀዳሚ ስራቸው እንዲሆን አቅጣጫ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ባካሄደው 20ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ከፕሬዚዳንቱ በተጨማሪ ሥድስት ሥራ አስፈፃሚ በመምረጥ ተጠናቋል።
