
በስልጠናው መክፈቻ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሸዋንግዛው ተባባል ባደረጉት ንግግር “የአካል ብቃት ምዘናውን በስኬት አልፋችሁ እዚህ በመገናኘታችን ደስ ብሎኛል። ሁለቱን ኢንስትራክተሮች በማግኘታችን በእውነት እድለኞች ነን፤ እናንተ ከፊፋ ከፍተኛ አሰልጣኞች መካከል ግንባር ቀደም ናችሁ። ስለዚህ ዳኞች ከዚህ ኮርስ እስከ ጥግ እንዲጠቀሙበት እመክራለሁ፤ ማድረግ የምትችሉትን ያህል ከፍተኛ ጥረት አድርጉ። ጥሩ እና አዝናኝ አምስት ቀናት ይኖረናል ብዬ አስባለሁ፤ መልካሙን ሁሉ እመኝላችኋለሁ” ብለዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ባሕሩ ጥላሁን በበኩላቸው ለኮርሱ ኢንስትራክተሮች “ወደ ሁለተኛ ሀገራችሁ ኢትዮጵያ እንኳን ደህና መጣችሁ” ካሉ በኋላ በዚህ ዓመት ህይወታቸውን ላጡ ኮሚሽነሮች እና ዳኞች የአንድ ደቂቃ የሕሊና ጸሎት በማስደረግ ንግግራቸውን ቀጥለዋል። አቶ ባሕሩ አክለውም “በሀገራችን የዳኝነት እድገት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀየረ ነው። ይህ የዳኞች ኮሚቴ ወደ ኃላፊነት ከመጣ ወዲህ የሚችሉትን ያህል ለማድረግ ሞክረዋል። በኢትዮጵያ ዳኝነት ውስጥ ሙያተኝነትን ለማሳደግ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። ይህ በፌዴሬሽናችን ውስጥ የወሰድነው በጣም ትልቅ እርምጃ ነው። የዳኝነት እድገቱን በጥሩ መንገድ ላይ ለማስገባት ትልልቅ ውሳኔዎችን በመወሰናቸው የዳኞች ኮሚቴውን እንደገና ማመስገን እፈልጋለሁ” ብለዋል።

የኮርሱ አስተባባሪና የዳኞች ዲፓርትመንት ዳይሬክተሩ አቶ ሙሉጌታ ምስጋናው ስልጠናው እውን እንዲሆን አስተዋጽኦ ላደረጉ በፌዴሬሽኑ የሚገኙ የተለያዩ ክፍሎች እንዲሁም ለተሳታፊዎች የተሟላ ትጥቅ ያቀረበውን ጎፈሬን አመስግነዋል።

የሴካፋ የዳኞች ኃላፊ ዓሊ ሙሐመድ ፌዴሬሽኑ፣ የዳኞች ኮሚቴው እንዲሁም ዲፓርትመንቱ ይህን እድል በአግባቡ ለመጠቀም ያደረጉትን ጥረት አድንቀዋል። ዓሊ ሙሐመድ አክለውም “በዋና ጸሐፊው ፊት መጥቀስ የምፈልገው ነገር ቢኖር ዘንድሮ እና ያለፈው ዓመት ለአፍሪካ ዳኞች በአካል ብቃት በኩል ጥሩ ነበር። ቢያንስ 8፣ 7፣ 9 የፊፋ ዳኞች የሚወድቁባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፤ ይህም በሀገራቱ ውስጥ ትልቅ ችግር ይፈጥራል። በዚህም ካፍ እና ፊፋ ከአካል ብቃት አሰልጣኞች ኃላፊዎች ጋር ተነጋግረው አሰልጣኝ ወደ ሀገሪቱ እንዲልኩ እና ዳኞቹን እንደገና እንዲፈትሹ መጠየቅ ይኖርባቸዋል። አሁን ግን በኢትዮጵያ ምንም አይነት ችግር የለብንም፤ ስለዚህ ለዚያ ማጨብጨብ እንችላለን። ይህ በዋዛ የመጣ ሳይሆን በብቁ ባለሙያዎቻችሁ የተሰራ ጠንካራ ሥራ ነው፤ ለአፍሪካም በጣም ጥሩ አርአያ ነው” ብለዋል።

ይህ ስልጠና እስከ ሰኞ ነሐሴ 25 ቀን 2018 ዓ.ም. የሚቀጥል ሲሆን ዛሬ ረፋድ በተካሄደው የአካል ብቃት ምዘና ከተፈተኑት 31 የጨዋታ አመራሮች መካከል ሁሉንም የፊፋ ዳኞች ጨምሮ ምዘናውን ማለፍ የቻሉ በአጠቃላይ 30 ተሳታፊዎች ስልጠናውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ።
ስልጠናውን በዋነኝነት የሚሰጡት የቴክኒካል ኢንስትራክተር ዓሊ አህመድ እና የአካል ብቃት ኢንስትራክተር መሐሙድ ሁሴን ጋቦኒ ናቸው።
