
በታንዛንያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ማጣሪያ ውድድር የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለውድድሩ ቅድመ ዝግጅት ጥሪ የተደረገላቸው 40 ተጫዋቾችን በመያዝ በዛሬው ዕለት ናሽናል ካምፒንግ ጀመራ’ሯል።
የ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ቤንጃሚን ዚመር ይመሩታል። አሰልጣኝ ዚመር ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን በማሰልጠን ቡድናችን በሴካፋ ውድድር 3ኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅና ከ22 ዓመታት በኋላ ለ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፍ ያደረጉ ሲሆን በውድድሩም ቡድናችን ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከጫፍ ደርሶ እንደነበር ይታወሳል።
በምክትል አሰልጣኝነት የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና በተለያዩ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታላላቅ ክለቦች ተጫውቶ ያሳለፈው ፍፁም ገብረማርያም የተሾመ ሲሆን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም በፕሪምየር ሊግ እና ከፍተኛ ሊግ ክለቦች ተጫውቶ ያሳለፈውና በጅማ አባ ቡና እንዲሁም በመቻል (ከ17 ዓመት በታች ቡድን) በግብ ጠባቂ አሰልጣኝነት የሠራው ገመቹ በቀለ በግብ ጠባቂ አሰልጣኝነት የሚሠራ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን የቴክኒክ አማካሪ እና ተጠባባቂ ቴክኒክ ዳይሬክተር አምሳሉ ፋንታሁን የአሰልጣኞችን ምርጫ ሂደትን በተመለከተ እንደገለፁት “የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በወጣቶች ልማት ፕሮጀክት ላይ ትኩረት አድርጎ በመሥራት ላይ ይገኛል። ከዚህ ጎን ለጎንም ለአሰልጣኞች ልማትም ትልቅ ትኩረት በመስጠት የቀድሞ ተጫዋቾች በብሔራዊ ቡድኖች ውስጥ እድል አግኝተው ልምዳቸውን እንዲቀስሙ እየተደረገ ነው። ዋናው አላማችን የተጫዋቾችን አቅም ማዳበር ብቻ ሳይሆን አሰልጣኞችንም እድል በመስጠት በመሆኑ የቀድሞ ተጫዋቾች በብሔራዊ ቡድኖች ውስጥ እድል አግኝተው ልምዳቸውን እንዲቀስሙ እየተደረገ ነው። ከዚህ ቀደም በሴካፋ ከ17 ዓመት በታች ውድድር ላይ በሪጅናል እና በናሽናል ካምፖች እንዲሁም በሴካፋ ውድድር ላይ ከክልል እና ከአዲስ አበባ ለተውጣጡ አሰልጣኞች እድል ሰጥተናል። በቅርቡም በአፍሪካ ዋንጫው ላይ ለቀድሞ ተጫዋቾች ፍቅሩ ተፈራ እና ሚካኤል ወልደሩፋኤል እድል የሰጠን ሲሆን አሁን ደግሞ ለፍፁም ገብረማርያም እና ለገመቹ በቀለ እድሉን ሰጥተናል። ሁለቱም በተጫዋችነት ያሳለፉ ከመሆኑ በተጨማሪ የአሰልጣንነት ኮርስ የወሰዱ በመሆኑ ይህን እድል አግኝተዋል። ወደፊትም ለሌሎች አሰልጣኞች ተመሳሳይ እድሎች የምናመቻች ይሆናል።” ብለዋል።
አምሳሉ ፋንታሁን አጠቃላይ የፌዴሬሽኑ የረጅም ጊዜ አላማ እነዚህ እድል እየተሰጣቸው የሚገኙ አሰልጣኞች ራሳቸውን በማሳየት እና በማሳደግ በቀጣይ የሀገሪቱን ታዳጊ እና ወጣት እንዲሁም ዋናውን ብሔራዊ ቡድኖች ሙሉ ለሙሉ ተረክበው በብቃት እንዲመሩ ማድረግ መሆኑን አብራርተዋል።
