ትዕግስት አሰፋ ፅ እና የጉዬ አዶላ አስደናቂ ድል በበርሊን ማራቶን አስመዘገቡ

52ኛው የበርሊን ማራቶን በሴቶችና በወንዶች ዘርፍ በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ተጠናቋል።
አትሌቶቻችን ባሳዩት አስደናቂ ብቃት፣ ፅናትና ጠንካራ ፉክክር በዓለም ከፍተኛ ከሚባሉት የማራቶን ውድድሮች አንዱ የሆነውን የበርሊን ማራቶን በድል አጠናቀዋል።
በሴቶች ዘርፍ ጀግናዋ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትዕግስት አሰፋ በአስደናቂ ፅናት የበርሊን ማራቶንን አሸንፋለች።
ትዕግስት አሰፋ በውድድሩ ከፍተኛ ፍጥነትና ብቃት በማሳየት አዲስ የዓለም ክብረወሰን (World Record) ለማስመዝገብ እየተፎካከረች ቆይታለች።
ሆኖም ባጋጠማት ጉዳት የዓለም ክብረወሰን የመስበር ዕቅዷን ማሳካት አልቻለችም።

ነገር ግን ጀግናዋ አትሌት በጉዳቱ ሳትበገር እስከመጨረሻው በፅናት በመታገል ውድድሩን በአሸናፊነት አጠናቃለች።
በዚህም በበርሊን ማራቶን ያላትን የበላይነት በማስቀጠል ለሦስተኛ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ሆናለች።
ይህ ድል የትዕግስት አሰፋን ተሰጥኦ፣ ቁርጠኝነትና የውድድር ፅናት ያሳየ ታላቅ የስኬት ታሪክ ሆኗል።
አትሌት ትዕግስት አሰፋን ተከትሎ በዳቱ ሂርፓ 2፡16፡53 በመግባት 2ኛ ደረጃን፣አትሌት ደራ ዲዳ 2፡16፡55 በመግባት 3ኛ ደረጃን ይዘዋል።
በተጨማሪም አትሌት በቀለች ጉዴታ 2፡18፡58 በመግባት 4ኛ፣አትሌት አለሚቱ ታሪኩ 2፡19፡01 በመግባት 5ኛ፣አትሌት ምስጋና አለማየሁ 2፡20፡27 በመግባት 7ኛ እንዲሁም አትሌት አሚነት አህመድ 2፡21፡45 በመግባት 10ኛ ደረጃን ይዘው ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

በወንዶች ዘርፍ ደግሞ አትሌት ጉዬ አዶላ 2፡02፡51 በሆነ ጊዜ በመጨረስ የግል ምርጥ ሰዓቱን በማስመዝገብ የውድድሩ አሸናፊ ሆኗል።
ይህ ለጉዬ አዶላ የበርሊን ማራቶንን ለሁለተኛ ጊዜ የማሸነፍ ስኬት ነው።

በወንዶች ዘርፍ ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም አስደናቂ ውጤት አስመዝግበዋል፦
- ገመቹ ዲዳ 2፡03፡19፣ 2ኛ ደረጃ
- ጌታነህ ሞላ 2፡04፡05፣ 4ኛ ደረጃ
- ሰለሞን ባረጋ 2፡04፡58፣ 5ኛ ደረጃ
- አሰፋ ቦኪ 2፡05፡32፣ 6ኛ ደረጃ
- አንዱአምላክ በልሁ 2:05.55፣ 7ኛ ደረጃ
- ሹራ ቂጣታ 2፡06፡04፣ 8ኛ ደረጃ
- ታዱ አባተ 2፡07፡16፣ 10ኛ ደረጃ
በዚህም 52ኛው የበርሊን ማራቶን በሁለቱም ፆታ በኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸናፊነት ተጠናቋል።
ትዕግስት አሰፋ በሴቶች ዘርፍ፣ ጉዬ አዶላ ደግሞ በወንዶች ዘርፍ በማሸነፍ የኢትዮጵያን የማራቶን ብቃት በዓለም መድረክ አሳይተዋል።
