የካፍ ገለልተኛ የገምጋሚዎች ቡድን የሀዋሳ ስታዲየም እና የከተማውን የማስተናገድ አቅም ሲገመግም ውሏል

በጉብኝቱ ላይ የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የገንዘብ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዳዊት ሀዬሶ፣ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ እንዲሁም የክልሉና የከተማዋ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የካፍ ባለሙያዎች ቡድን ሀዋሳ ስታዲየምን በተመለከተ ባደረጉት ምልከታ ሪፖርት አቅርበዋል። በምልከታቸውም ስታዲየሙ ማሻሻያ ለማድረግ የሚያስችል ሰፊ ክፍት ቦታዎች እንዳሉት ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ እድሳት እንደሚገባው፣ ስታዲየሙ እና የልምምድ ሜዳው የእድሳት ሥራ በአንድ ዓመት ውስጥ ሊጠናቀቁ እንደሚገባ አንስተዋል። ስታዲየሙ ዲዛይኑ በጥሩ ሁኔታ የተሰራ ቢሆንም ማሻሻያ መደረግ አለበት የሚል ሀሳብ ቀርቧል።

በተጨማሪም የቀረበው የበጀት ቁጥር ዳግመኛ መታየት እንዳለበትና ከፍ በማድረግ በአጭር ጊዜ በሙሉ ኃይል ከፍተኛ ሥራ ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ የጎበኙ ሲሆን ሜዳው እና መልበሻ ክፍሉ መዋቅር ጥሩ በመሆኑ ማሻሻያ ለማድረግ እንደሚጠቅም አስተያየት ሰጥተዋል። አርቲፊሻል ሜዳው ሙሉ ለሙሉ መነሳት እንዳለበት እና የመልበሻ ክፍቶቹ በአዲስ መልክ መሠራት እንዳለባቸው ተገልጿል።
በአጠቃላይ የካፍ ባለሙያዎች ቡድን የስታዲየሙን እና የአካባቢውን አጠቃላይ ሁኔታ በመገምገም በቀጣይ መደረግ ስለሚገባቸው ዝግጅቶች አስተያየታቸውን ሰጥተው ሌሎች የከተማው መሠረተ ልማቶች እና ሆስፒታሎች ጎብኝተዋል።
