
የኢትዮጵያ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን 4ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአዲስ አበባ ከተማ አካሂዷል። ጉባኤው የኦዲትና የስራ ሪፖርቶችን መርምሮ በማጽደቅ፣ የ2019 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ተወያቶ በማፅደቅ እና አዳዲስ የስራ አስፈፃሚ አባላትን በመምረጥ ተጠናቋል።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሳቦም አበራ ሚልኬሳ በጉባኤው መክፈቻ ባደረጉት ንግግር ፌዴሬሸኑ ባላፉት ዓመታት የቴኳንዶ ስፖርትን ለማስፋፋትና ለማሳደግ ለክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ድጋፍ በማድረግ በዘረጋው የውድድር መርሀ ግብር በሀገር አቀፍ የክለቦች ሻምፒዮናዎችን፣ የግል እና የቡድን ውድድሮችን በዕድሜና ክብደት ደረጃ በማካሄድ ዉጤታማ ስራዎችን እንደሰራ አውሰተዋል።

በማከልም ሳቦም አበራ የኢትዮጵያ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ለአሰልጣኞች፣ ለዳኞች እና ለስፖርተኞች የሙያ ማሻሻያ እና የቴክኒክ ስልጠናዎችን በመስጠት አንድ ወጥ የአሰራር ደረጃ በመፍጠር በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሀገራቸውን የሚወክሉ ብሔራዊ የቴኳንዶ ቡድኖችን መምረጥና ማዘጋጀት እንደቻለ ገልፀዋል።
በጉባኤው የተሳተፉ አካላት በበኩላቸው ፌዴሬሸኑ በሚቀጥሉት ዓመታት ከሚመለከተው አካል ጋር በመተባበር የቴኳንዶ ስፖርት በሀገራችን በተዘረጋው የታዳጊ ወጣቶች የምዘናና የውድድር መርሀ ግብር ተካቶ ተተኪ ስፖርተኞች እንዲፈሩበት በትኩረት እንዲሰራ፣ የሀገር ውስጥ ውድድሮችን በማብዛት ዓለም አቀፍ የውድድር ተሳትፎን እንዲያሳድግ እና ፌዴሬሸኑን ገቢ የሚያሰስገኙ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ እንዲሰራ ጠይቀዋል።

ጉባኤው ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት የኢትዮጵያ ቴኳንዶ ፌዴሬሸንን የሚመሩ ስራ አሰፈፃሚዎችን ለመምረጥ የፌዴሬሸኑን ህግና ደንብ መሰረት በማድረግ በሰጠው ድምፅ ለሁለተኛ ዙር ሳቦም አበራ ሚልኬሳን በፕሬዚዳንትነት በሙሉ ድምፅ ሲመርጥ በስራ አስፈፃሚነት አቶ ከድር አህመድ፣ አቶ ተገኑ በቀለ፣ አቶ መኪ ገመቹ ፣ ወ/ሮ አስቴር ደርበው፣ ወ/ሮ ማዓዛ ጋሻው እና ወ/ሮ በዓል ግርማቸውን መርጧል።
ተመራጮቹም ጉባዔው እምነት ጥሎ ለሰጣቸው ድምፅ በመታመን ለስፖርቱ እድገት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።
በመጨረሻም የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ከበደ እጅጉ 4ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሄደው የኢትዮጵያ ቴኳንዶ ፌዴሬሸን እንደ ሃገር የሚያከናውናቸው ማሕበራዊ አበርክቶዎች የሚደነቅ መሆኑን በመግለፅ በዛሬው እለት ያካሄደው ጉባኤም በጉባዔተኞች የነቃ ተሳትፎ የደመቀ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ምርጫ የተደረገበት መሆኑን ተናግረው ፌዴሬሽኑ በቀጣይ የሚያከናውናቸው ተግባራት በስትራቴጅክ እቅድ ተደግፈው ጉባኤተኛው ያነሳቸው ሀሳቦች በግበዓትነት ተይዘው የሚተገበሩ እንዲሆኑ አሳስበዋል።
