
በኢትዮጵያ ቴኳንዶ ፌዴሬሸን አዘጋጅነት ሲካሄድ የቆየው የክለቦች ሻምፒዮና እና የሙያ ማሻሻያ ስልጠና ተጠናቋል።
ፌዴሬሽኑ ባካሄደው ሻምፒዮና እና የሙያ ማሻሻያ ስልጠና ላይ ከክልልና ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ ክለቦች እና ስፖርተኞች ተሳትፈዋል።
ፌዴሬሽኑ ከክለቦች ሻምፒዮና ጎን ለጎን በንድፈ ሀሳብና በተግባር የተደገፈ የሙያ ማሻሻያ ስልጠናዎችን ለተከታታይ ቀናት ሰጥቷል።

የሙያ ማሻሻያ ስልጠናውም ሰልጣኞች ወደ እየመጡበት አካባቢ ሲመለሱ በስልጠናው የወሰዱትን እና ያዳበሩትን እውቀት ተግባራዊ እንዲደርጉ ያግዛቸዋል።
ፌዴሬሽኑ ባካሄደው ሻምፒዮና ዋን ላቭ ቴኳንዶ ክለብ፣ ብላክ ጃጋሪ ቴኳንዶ ክለብ እና ኑር ታለንት ቴኳንዶ ክለብ ከ1-3 ያለውን ደረጃ በመያዝ የወርቅ፣ የብርና የነሀስ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆነዋል።
በልዩ ፓተርን ኑር ታለንት ክለብ ሲሻለም ጋምቤላ ክልል ስፔሻል ተሸላሚ ሆኗል። የኢትዮጵያ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን በሻምፒዮናው ከመቶ ሺህ እስከ15ሺ ብር ከ1-5 ለወጡ ክለቦች ሽልማት አበርክቷል።

የቴኳንዶ ስፖርት በማህበረሰቡ በተለይም በወጣቶች ዘንድ ተወዳጅና ተዘውታሪ እየሆነ መምጣቱ ስፖርቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መጥቷል።
ስፖርቱን በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ከስልጠናና ውድድር ባሻገር በሁሉም ቦታ የክትትልና ድጋፍ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል።
ፌዴሬሽኑ በአዲስ አበባ ከተማ እያካሄደ ባለው ስልጠናና ውድድር ከ1500 በላይ የቴኳንዶ ስፖርተኞች ማሳተፍ ችሏል።
በሻምፒዮናው የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ስፖርተኞች ሀገራቸውን ወክለው በዓለምአቀፍ ደረጃ ውድድር ተሳታፊ ይሆናሉ።
በስፖርት ማህበራት መመሪያና ህግ መሠረት የስፖርት ማህበራት ሲቋቋሙ በፍይናንስ ራሳቸውን በመቻል በዓለምአቀፍ ደረጃ ሀገርን የሚያስጠሩ ስፖርተኞችን እንዲያፈሩ ይደነግጋል።
