
በአርጀንቲና ቦነስ አይረስ በተካሄደው የግማሽ ማራቶን ውድድር በወንዶች አዲስ የዓለም ክብረወሰን ያስመዘገበው ጀግናው አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ እና በሴቶች የውድድሩን አዲስ የቦታ ክብረወሰን በማስመዝገብ ያሸነፈችው ጀግናዋ አትሌት ፎቴን ተስፋይ ዛሬ ማታ አዲስ አበባ ገብተዋል።

በዚህም ከፍተኛ የስፖርት ድል ይዘው ወደ አገራቸው ለተመለሱት ሁለቱ ጀግኖች አትሌቶች በቦሌ ዓለም አቀፍ አሮፕላን ማረፊያ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ 56:51 በሆነ ጊዜ በመግባት፣ በዩጋንዳዊው አትሌት ጃኮብ ኪፕሊሞ ተይዞ የነበረውን 57:20 የዓለም ክብረወሰን በማሻሻል አዲሱን የዓለም ምርጥ ሰዓት አስመዝግቧል።
በሴቶች ውድድር ደግሞ አትሌት ፎቴን ተስፋይ 1:03:57 በሆነ ጊዜ በመግባት የውድድሩን የቦታ ክብረወሰን በማሻሻል በአንደኝነት አሸንፋለች።

ሁለቱ ጀግኖች አትሌቶቻችን አዲስ አበባ ሲገቡ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ መኪዩ መሐመድ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን፣ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ኢንጅነር ጌቱ ገረመው፣ የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አትሌት የማነ ፀጋይ፣ የፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር አመንሲሳ ከበደ፣ አሰልጣኝ ገመዶ ደደፎን ጨምሮ አሰልጣኞች፣ የአትሌቶቹ ቤተሰቦችና ታዋቂ አትሌቶች በተገኙበት፣ በፌዴራል ፖሊስ ማርሽ ባንድ አጃቢነት ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
