
በሳምንቱ መጨረሻ በተለያዩ ሀገራት በተካሄዱ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አስደናቂ ውጤቶችን አስመዝግቧል ።
በሰሜን አየርላንድ ላርን ከተማ በተካሄደው Antrim Coast Road Race ውድድር፣ በዚህ ዓመት አዲስ በተጨመረው የ5 ኪሎ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያውያን የበላይነታቸውን አሳይተዋል።
በሴቶች 5 ኪሎ ሜትር ውድድር አትሌት አይናዲስ መብራቱ ርቀቱን በ14 ደቂቃ ከ51 ሰከንድ በማጠናቀቅ የውድድሩ አሸናፊ ሆናለች።
በወንዶች 5 ኪሎ ሜትር ደግሞ አትሌት ኤርሚያስ ግርማ በ13 ደቂቃ ከ50 ሰከንድ በማጠናቀቅ አንደኛ ደረጃ በመያዝ አሸንፏል ።
በዚሁ ውድድር የሴቶች 21 ኪሎ ሜትር ግማሽ ማራቶን ላይ አትሌት ግርማዊት ገብረእግዚአብሔር በ1 ሰዓት 6 ደቂቃ ከ12 ሰከንድ በማጠናቀቅ አንደኛ ሆናለች።
አትሌት ውዴ ከፍያለው ደግሞ 1 ሰዓት 7 ደቂቃ ከ12 ሰከንድ በመግባት ሦስተኛ ደረጃን ይዛለች።
በወንዶች ግማሽ ማራቶን አትሌት ይስማው ድሉ 1 ሰዓት 1 ደቂቃ ከ5 ሰከንድ በማስመዝገብ አምስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
በፓላንድ ሲሊሲያ ዳይመንድ ሊግ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል።
በወንዶች 3,000 ሜትር መሰናክል አትሌት ገመቹ ጎዳና ርቀቱን በ8 ደቂቃ ከ2 ሰከንድ በማጠናቀቅ አንደኛ ደረጃን ይዞ የውድድሩ አሸናፊ ሆኗል።
በሴቶች 1,500 ሜትር አትሌት ፅጌ ዱጉማ 3 ደቂቃ ከ55 ሰከንድ በሆነ ውጤት በአስደናቂ አጨራረስ የውድድሩን ድል ተቀዳጅታለች።
በሴቶች 5,000 ሜትር ደግሞ አትሌት ፍሬወይኒ ሀይሉ ርቀቱን በ14 ደቂቃ ከ54 ሰከንድ በማጠናቀቅ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
