መዋቅራዊ እውርነት፦ የአፍሪካ ስፖርት ጋዜጠኞች በዓለም አቀፍ መድረኮች የሚገጥማቸው የቪዛ አድልዎ እና የማርካ ኢትዮጵያ ጽኑ አቋም

0
Screenshot_2026_1001_133912~3

ትላልቅ ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች ሲዘጋጁ “ዓለምን በአንድነት የሚያገናኙ” እና “ሁሉንም ያካተቱ” መሆናቸው በስፋት ይሰበካል። ነገር ግን ከእነዚህ አንጸባራቂ መፈክሮች ጀርባ፣ በተለይም ከአፍሪካ ለሚጓዙ የስፖርት ጋዜጠኞች የሚዘረጉት መዋቅራዊ እና ቢሮክራሲያዊ መሰናክሎች የብዙዎችን ተስፋ የሚያስቆርጡ እና ሙያዊ እኩልነትን የሚጋፉ ናቸው።

የዘንድሮው የሮተርዳም 2026 ዓለም አቀፍ የአርቲስቲክ ጅምናስቲክስ ሻምፒዮና አዘጋጆች ለጋዜጠኞች የላኩት የቪዛ ድጋፍ ደብዳቤ የዚህ መዋቅራዊ እውርነት ዓይነተኛ ማሳያ ሆኖ ተመዝግቧል። አዘጋጆቹ በደብዳቤያቸው ላይ “ማንኛውም የጉዞ፣ የሆቴል ማረፊያ እና የሕክምና ኢንሹራንስ ወጪ በጋዜጠኛው ወይም በላከው ተቋም ይሸፈናል” የሚል አስገዳጅ ዓረፍተ ነገር በግልጽ አስፍረዋል ።

“እኩልነት” ወይስ “መዋቅራዊ አድልዎ”?

ይህንን መደበኛ አሠራር (Template) ከአውሮፓ እና ከአፍሪካ ጋዜጠኞች ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ስንመዝነው ፍጹም ፍትሃዊነት የጎደለው መሆኑን እንረዳለን።

  • የአውሮፓ ጋዜጠኞች፦ ምንም ዓይነት የቪዛ ገደብ የለባቸውም፤ በአጭር ርቀት በባቡር ተጉዘው፣ የፈለጉትን የቤት ኪራይ (Guest House) አማራጭ ተጠቅመው ከ500 ዩሮ ባነሰ ወጪ ውድድሩን መታደም ይችላሉ።
  • የአፍሪካ (የኢትዮጵያ) ጋዜጠኞች፦ ለአየር ትኬት ብቻ ከ310,000 ብር በላይ መድበው፣ የአውሮፓ ኤምባሲዎችን ጥብቅ የቪዛ መስፈርት መጋፈጥ ይኖርባቸዋል።

በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እያለ፣ በቪዛ ድጋፍ ደብዳቤው ላይ “ወጪውን ራሱ ይሸፍናል” የሚል ቀጥተኛ ጽሑፍ ማስፈር፣ በሼንገን ኤምባሲዎች ፊት ለአፍሪካውያን ጋዜጠኞች ቀጥተኛ የቪዛ መከልከያ ምክንያት (Automatic Visa Denial) መፍጠር ማለት ነው። ይህንን የገንዘብ መረጃ በደብዳቤው ላይ በግልጽ ከመጻፍ ይልቅ በውስጥ ኢሜል ማሳወቅ እየተቻለ፣ አውነታዊ (Template) አሠራርን ብቻ ሙጥኝ ማለት የጋዜጠኞችን ነባራዊ ችግር ካለመረዳት የሚመጣ ግድየለሽነት ነው።

የማርካ ኢትዮጵያ ጽኑ አቋም እና ዓለም አቀፉ ቅሬታ

የማርካ ኢትዮጵያ ስፖርት ሚዲያ (Marca Ethiopia Sports Media) ዋና አዘጋጅ ወሰንሰገድ መርሻ ደሚሴ፣ ይህንን አድሏዊ አሠራር በጽኑ በመቃወም ሙያዊ ቅሬታውን ለዓለም አቀፉ ጅምናስቲክስ ፌዴሬሽን (FIG) አቅርቧል ። አዘጋጆቹ መጀመሪያ ላይ የፈጠሩትን የስም ስህተት አምነው ይቅርታ የጠየቁና ደብዳቤውን በትክክል ያስተካከሉ ቢሆንም ፣ መዋቅራዊ የአጻጻፍ ፖሊሲያቸውን ለመቀየር ግን ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

የኢትዮጵያ ጅምናስቲክስ ፌዴሬሽንም (በጽሕፈት ቤት ኃላፊው በአቶ ሰለሞን በኩል) የተወሰደውን አቋም ሙሉ በሙሉ በመደገፍ፣ የአዘጋጁ አገር ቢያንስ ለአፍሪካውያን ጋዜጠኞች የማረፊያ (Accommodation) ምቹ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደነበረበት እና ውሳኔው ትክክል መሆኑን አረጋግጧል።

ማርካ ኢትዮጵያ ከአውሮፓውያን ጋዜጠኞች ጋር እኩል የማይታይበትን፣ ለቪዛ መከልከል ምክንያት የሚሆንን ደብዳቤ ይዞ በኤምባሲዎች ደጅ ከመንከራተት ይልቅ፣ የ10 ዓመታት የውጭ ዓለም አቀፍ የጋዜጠኝነት ልምዱን እና ሙያዊ ክብሩን አስጠብቆ የቀረበለትን የውድድር ግብዣና ፈቃድ (Accreditation) በኩራት እንደማይቀበልና እራሱን ማግለሉን በይፋ አሳውቋል።

ጉዳዩ እዚህ ላይ ብቻ አላበቃም፤ ማርካ ኢትዮጵያ ይህ በአፍሪካውያን ጋዜጠኞች ላይ የሚፈጸመው መዋቅራዊ ተጽዕኖ ሥር ነቀል መፍትሔ እንዲያገኝ፣ የተፈጠረውን ሙሉ ዝርዝር ችግር እና ተጨባጭ ማስረጃዎችን በማያያዝ ለዓለም አቀፉ የስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር (AIPS) እና ለአፍሪካ ስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር (AIPS Africa) ይፋዊ የቅሬታ እና የጥቆማ ደብዳቤ (Official Complaint & Advocacy Letter) ልኳል ።

ዓለም አቀፍ ተቋማት ለወደፊቱ ከድሀ ሀገሮች ማለትም ከደቡብ ንፍቀ ክበብ (Global South) ለሚመጡ ጋዜጠኞች ምቹ እና ፍትሃዊ የሆነ አሠራር ካልዘረጉ፣ የስፖርት ሚዲያው ዓለም አቀፋዊ ተደራሽነት የአንድ ወገን ብቻ ሆኖ ይቀራል። ማርካ ኢትዮጵያ ግን ከቢሮክራሲያዊ አድልዎ ይልቅ ለሙያዊ ክብሩ ቅድሚያ መስጠቱን ይቀጥላል!ይህ አይነቱ ተቃውሞ መግለጽና ለስፖርት ጋዜጠኞች መታገል የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ቢሆንም ማርካ ኢትዮጵያ ስፖርት ግን የጉዞም ሆነ የሀገሪቱ ጋዜጠኞች የሚደርሳባቸውን ቢሮክራሲያዊ አሰራር የውጭ ጋዜጠኞችን ለግብዣ ሳትል ሳትለማመጥ ትግሏን ትቀጥላለች።

Facebooktwitterlinkedinyoutubetumblrinstagramflickrfoursquaremail
Facebooktwitterredditpinterestlinkedintumblrmail