የዓለም አትሌቲክስ ከታላላቅ ዓለም አቀፍ የስፖርት ተቋማት ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት የሕፃናት አትሌቲክስ ፕሮግራምን ይበልጥ ሊያጠናክር ነው

0
6ad87bf6356b2e41e1f8a6da

የዓለም አትሌቲክስ (World Athletics) በኢሜል ባደረሰን መልዕክ የሕፃናት አትሌቲክስ (Kids’ Athletics) ፕሮግራም በማኅበረሰብ ላይ የሚያመጣውን በጎ ተፅዕኖ ይበልጥ ለማሳደግ “Global Sport for Good Initiative” ከተሰኘው ዓለም አቀፍ ጥምረት ጋር በጋራ መሥራት መጀመሩን አስታወቀዋል ። ይህ ተነሳሽነት ከዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (IOC)፣ ከዓለም ራግቢ፣ ከዓለም የቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን (FIBA) እና ከዓለም ባድሚንተን ፌዴሬሽን (BWF) ጋር በጋራ የሚተገበር ታላቅ ጥምረት መሆኑንም ገልጿል።

ከ2024 ጀምሮ ተግባራዊ መሆን የጀመረው ይህ ዓለም አቀፍ ተነሳሽነት፣ ስፖርትን እንደ መሣሪያ በመጠቀም የሕፃናትን ጤና፣ ማካተትን፣ ትምህርትን እና የማኅበረሰብ ልማትን ማሳደግ ላይ ትኩረት ያደርጋል። ፕሮግራሙ ዕድሜያቸው ከ4 እስከ 14 ዓመት የሆኑ ሕፃናትን እና ታዳጊዎችን የሚያካትት ሲሆን፣ በቅርቡ በተደረገ ዘመቻ በ170 አገራት ውስጥ ከ7 ሚሊዮን በላይ ሕፃናትን ማሳተፍ ችሏል።

የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዝዳንት ሰባስቲያን ኮ (Sebastian Coe) ስለ ተነሳሽነቱ ሲናገሩ፦ “የሕፃናት አትሌቲክስ ከተሳታፊዎች ቁጥር ባሻገር ስፖርቱ በወጣቶች እና በማኅበረሰባቸው ሕይወት ላይ የሚያመጣውን ትክክለኛ ለውጥ ለመረዳት ትልቅ ዕድል ይሰጠናል። ስፖርት ማኅበረሰብን የማስተሳሰር ታላቅ ጉልበት አለው” ብለዋል።

ይህንን ፕሮግራም በመሬት ላይ ለማስፈጸም 18 ዋና አሰልጣኞች (Master Trainers)፣ ከ300 በላይ የብሔራዊ ፌዴሬሽን መሪ አስተማሪዎች እና ከ10,000 በላይ አሰልጣኞችና መምህራን በክለብና በትምህርት ቤት ደረጃ ይሳተፋሉ። አሰልጣኞችን በቴክኖሎጂ ለመደገፍም ባለፈው ኤፕሪል ወር ላይ “Kids’ Athletics app” የተሰኘ መተግበሪያ በ6 ቋንቋዎች በነፃ እና ያለ ኢንተርኔት (offline) መሥራት በሚችል መልኩ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

ይህ አዲስ ጥምረት ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የስፖርቱን ጠቀሜታ በተጨባጭ በመለካት ለአጋሮቻቸው፣ ለየአገራቱ መንግሥታት እና ለሚመለከታቸው አካላት ማስረጃ ይዘው እንዲያቀርቡ ትልቅ አቅም ይፈጥራል ተብሏል።

የዓለም አትሌቲክስ (World Athletics) ይህንን ዘመናዊ የሕፃናት አትሌቲክስ (Kids’ Athletics) በሚያካሂደው ፕሮግራም ላይም ኢትዮጵያ የዚህ ፕሮጀክት ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንደመትሆን ታውቋል። በኢትዮጵያ ውስጥ ከተለያዩ አካዳሚዎች እና ትምህርት ቤቶች ጋር በመተባበር ተግባራዊም እያደረገ ነው፣ ይሁንና ለኢትዮጵያ ብቻ በተለይ መልኩ የተመደበ የተወሰነ የገንዘብ መጠን (Specific Funding Amount) ይፋ አላደረገም።ይሁንና ቀጥተኛ ያልሆነ ድጋፍ (Indirect Funding) እያደረገ ይገኛል።

የገንዘብ ድጋፉ አሰጣጥ ሥርዓት (Funding Structure)

የዓለም አትሌቲክስ ለብሔራዊ ፌዴሬሽኖች (ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጨምሮ) በቀጥታ ትልቅ የገንዘብ ቼክ ከመስጠት ይልቅ፣ በጀቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለቴክኒክ ድጋፍ፣ ለአሰልጣኞች ማሰልጠኛ (Master Trainers)፣ ለስልጠና መተግበሪያዎች ልማት እና ለቁሳቁስ አቅርቦት በቀጥታ ያውለዋል።

ይህ በጀት የሚመጣው ከዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (IOC) እና ከሌሎች 4 ታላላቅ ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽኖች ጋር በጋራ ከተቋቋመው ማዕከላዊ ፈንድ በመሆኑ፣ ለእያንዳንዱ ሀገር የሚደርሰው ድጋፍ የሚለካው በገንዘብ ሳይሆን በሰለጠኑ ባለሙያዎች እና በተደራሹ ሕፃናት ቁጥር ነው።

ኢትዮጵያ በቴክኒክ ድጋፍ ያገኘችው ጥቅም

በቅርቡ በ6 ቋንቋዎች የበለጸገው እና ያለ ኢንተርኔት (Offline) መሥራት የሚችለው አዲሱ “Kids’ Athletics App” በኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ አሰልጣኞች እና የስፖርት መምህራን በነፃ ተደራሽ ሆኗል። ይህ መተግበሪያ የወረቀት ማተሚያ ወጪን ሙሉ በሙሉ ያስቀራል።

በፕሮጀክቱ ውስጥ ካሉት 300 በላይ የብሔራዊ ፌዴሬሽን መሪ አስተማሪዎች (Lead Educators) እና 10,000 አሰልጣኞች መካከል የኢትዮጵያ ባለሙያዎች የተካተቱበት ሲሆን፣ የዓለም አቀፍ ደረጃ ስልጠናዎችን በነፃ አግኝተዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሮግራሙ በሕፃናቱ ጤና እና ማኅበረሰብ ላይ የሚያመጣውን ለውጥ በሳይንሳዊ መንገድ ለክቶ ለመንግሥት እና ለአገር ውስጥ ስፖንሰሮች በማስረጃነት የሚያቀርብበትን የአቅም ግንባታ ድጋፍ እንደሚያስገኝለትም ተጠቁሟል።

Facebooktwitterlinkedinyoutubetumblrinstagramflickrfoursquaremail
Facebooktwitterredditpinterestlinkedintumblrmail