
የኢትዮጵያ ከ 17ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ወሳኝ መርሐ ግብሩን ዛሬ ከቀኑ 9:00 ከ ዛምቢያ አቻው ጋር ያደርጋል።

ብሔራዊ ቡድኑ 90 ደቂቃውን በአሸናፊነት ከተወጣ በሞሮኮው የአለም ዋንጫ ተሳታፊ መሆኑን ያረጋግጣል።
አሰልጣኝ ራውዲ አሊ « በትኩረት ለመጫወት ዝግጁ ነን » ያለች ሲሆን « የኢትዮጵያ ህዝብ እግር ኳስ ወዳድ ነው መጥቶ እንዲደግፈን ጥሪ አቀርባለሁ » ብላለች።
በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ዛምቢያ 2ለ1 በሜዳዋ ያሸነፈች ሲሆን በድምር ውጤት የሚያሸንፈው ቡድን ለአለም ዋንጫው ማለፉን ያረጋግጣል።
ጨዋታው ከቀኑ 9፡00 በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ሲካሄድ የእግር ኳስ ቤተሰብ በስታዲየሙ በነፃ በመታደም ታዳጊዎችን እንዲያበረታታና የዚህ ታሪካዊ ጨዋታ አካል እንዲሆን ፌዴሬሽኑ ጥሪ አቅርቧል።
ኢትዮጵያ ጨዋታውን በድምር ውጤት በበላይነት ካጠናቀቀች በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለሴቶች ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ታሳታፊ ትሆናለች።

በዛሬው የመልስ ጨዋታ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አረንጓዴ ማልያ፣ ቢጫ ቁምጣ፣ ቀይ ካሶተኒ ለብሰው ወደ ሜዳ የሚገቡ ይሆናል።

በሌላ በኩል ዛምቢያን የሚገጥመው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድናችን ዛሬ የሚያደርገውን ወሳኝ የ90 ደቂቃ ጨዋታ በተመለከተ ትናትና አስቀድሞ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የመጨረሻ ልምምዱን አከናውኗል። በልምምዱ ላይ የኢ/እ/ፌ ምክትል ኘሬዚዳንት ዳኛቸው ንግሩ (ዶ/ር)፣ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ባሕሩ ጥላሁን፣ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ወ/ሪት ብዙዓየሁ ጀምበሩና የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በመገኘት ቡድኑን አበረታተዋል።
