መንግስት በአገራችን አበረታች ቅመሞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ተገለፀ።

የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በጋራ የምክክር መድረክ አካሂደዋል።
የምክክር መድረኩ በአበረታች ቅመሞች መሰረታዊ ጉዳዮች እና በህግ ማዕቀፎች ዙሪያ ዓላማ ያደረገ ነው።
መንግስት በአገራችን አበረታች ቅመሞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ በምክክር መድረኩ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ፀረ አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርስ በሰጡት ማጠቃለያ የስፖርት ዘርፉን በተለይም አትሌቲክሱ ንፅህናው ሊጠበቅ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ መለያ የሆነውን አትሌቲክስ ከአበረታች ቅመሞች በመከላከል ንፅህናውን ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ሊተላለፍ እንደሚገባም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ለዚህም አትሌቱና የስፖርቱ ሙያተኛ የማይተካ ሚና እንዳለው በመግለፅ የህግ ጥሰት እንዳይኖር ሀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዶፒንግን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሁሉን አቀፍ ትብብር እንደሚያስፈልግ ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ ችግሩን ለመከላከል ፌዴሬሽኖች፣ ክለቦች፣ የአትሌቶች፣ ማናጀሮች እና አሰልጣኞች የላቀ ሚና እንዳላቸው ገልፀዋል።
አበረታች ቅመሞችን በዘላቂነት በመከላከልና በመቆጣጠር የአገራችንን መልካም ገፅታ ለማስጠበቅ እና የስፖርት ዲፕሎማሲ ግቦችን ለማሳካት እቅድ ተይዞ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።
ዶፒንግን ለመከላከል የስፖርት ፖሊሲ፣ የወንጀል ህግና የስፖርት አስተዳደር አዋጁን ጨምሮ በቂ የሆኑ የህግ ማዕቀፎች ወጥተው ወደ ትግበራ መግባታቸው በውይይቱ ተጠቁሟል።

በየደረጃው የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫና የህዝብ ንቅናቄ ተግባራት ተቀርፀው በመከናወን የህግ ጥሰት የሚፈፅሙ አካላትን በመለየት አስተማሪ የሆኑ የእርምት እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡
በዚሁ መሰረት እ.ኤ.አ በ2026 በየደረጃው በተካሄዱ ምርመራዎች 20 የሚሆኑ አትሌቶች በተለያየ መልኩ የአበረታች ቅመሞች የህግ ጥሰት መፈፀማቸው በውይይቱ ተመላክቷል
በአትሌቶቹም እንደየ ጥፋታቸው መጠን የተለያዩ የቅጣት ውሳኔዎ እንደተላለፈባቸው በውይይቱ ተገልጿል።
በተጨማሪም ከአትሌቶች ጀርባ በመሆን በህግ ጥሰቱ ውስጥ የተሳተፉ የተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማትም ተጠያቂ መደረጋቸውን በመድረኩ ላይ ተነግሯል፡፡

በቀጣይም መንግስት በአበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ ላይ ያለው አቋም እጅግ በጣም ጠንካራ መሆኑንና የወንጀል ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ስራም በትኩረት እንደሚሰራ በመድረኩ ተመላክቷል።
በውይይቱ የኢትዮጵያ ፀረ አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራሮች፣ አትሌቶች ፣አሰልጣኞች ፣የአትሌት ተወካዮች ተገኝተዋል።
